🔈#ጤና_ባለሙያዎች " ባለሙያው 'ርቦኛል፣ ረሃብ ጊዜ አይሰጥም ነው' ያለው። ስለዚህ አቅምም ከሌላቸው በግልጽ መናገር ነው። ድለላ ነው የደበረው ባለሙያው ” - ማኀበሩ

" ባለሙያው 'ርቦኛል፣ ረሃብ ጊዜ አይሰጥም ነው' ያለው። ስለዚህ አቅምም ከሌላቸው በግልጽ መናገር ነው። ድለላ ነው የደበረው ባለሙያው ” - ማኀበሩ
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ያደረጉት ቃለ ምልልስ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሊሆን አይችልም ብለው እንደሚያምኑ ባለሙያዎችና የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኀበር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ።
ባለሙያዎቹና ማኀበሩ ይህን ያሉት ሚኒስትሯ ከሰሞኑ ባደረጉት ገለጻ፣ ለጤና ባለሙያዎች በቀጣይ ዓመት ከፍ ያለ በጀት ለመበጀት በቂ ዝግጅት መደረጉን ጨምሮ የሰጡትን ማብራሪያ በተመለከተ ነው።
የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኀበር ምን አለ ?
“ እንደዚህ አይነት ምላሾች የተለመዱ ናቸው። ነግሮች ለተሾሙበት ስልጣናቸው ስጋት ሲሆኑባቸው በመንግስታዊ ሚዲያዎች ወጥተው መናገራቸው የተለመደ ነው።
ግማሹ አንቋሾ ይመልሳል፤ ፓለታካዊም ያደርጋል። ግማሹ ደግሞ 'እውነት ነው፤ ጥያቄያቸውን ተረድተነዋል ፤ ግን ሌላ አካል እንዳይዘውራቸው' ይላሉ። 
ጥያቄ እያቀረበ ያለው እስከ 20 ዓመት በትምህርት የቆየው ጤና ባለሙያ ነው። በዚህ ልክ በትምህርት ዝግጅት ያለፈን ባለሙያ ‘የማኀበራዊ ድረ ገጽ አክቲቪስቶች አእምሯቸውን ዋሽ አድርገውታል’ ብሎ መግለጽ በራሱ አሳፋሪ ነው።
ባለሙያዎች በቁጥር ጠቅሰው ጥያቄዎችን ጠይቀዋል። ግን በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚመለከታቸው አካላት በሚገባ እውቅና አልሰጡትም ‘ባለሙያው ጥያቄ ይኖረዋል፤ እውነት ነው’ ይበሉ እንጂ።
ጤና ሚኒስትሯ የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄ እውቅና ቢሰጡት ኖሮ የቀረቡ 12ቱንም ጥያቄዎች ማስረዳት ነበረባቸው። ይሄ ባለሙያ የሚናቅ አይደለም። ቀጥተኛ ምላሽ ቢሰጡበት ነው ምላሻቸውን የምናምነው።
ባለሙያው 'ርቦኛል፣ ረሃብ ደግሞ ጊዜ አይሰጥም' ነው ያለው። ስለዚህ አቅምም ከሌላቸው በግልጽ መናገር ነው። ባለሙያው ድለላ ነው የደበረው። አቅም የለንም እንዳይሉ ደግሞ አለን እያሉ ነው ” ብሏል።
ጤና ባለሙያዎችስ ምን አሉ ?
“ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አይተነዋል፤ ግን ለጥያቄያችን ምንም ምላሽ አላገኘንበትም።
ስለበጀት ማንሳት ካስፈለገ፣ በጀት መበደብ መብት ሳይሆን ግዴታ ነው።
ኢትዮጵያ የፈረመችው ስምምነት አለ በዓለም ጤና ድርጅት። ሪከመንድ የሚያደርገው አገሪቱ ከምትመድበው በጀት 15% ለጤና መበጀት አለባት ይላል። ይሄ ኢትዮጵያ የፈረመችው ነውና ያን ማክበር ነው ያለባቸው።
በ2017 ዓ/ም 3.7% ነው የመደቡት፤ በጤናው ዘርፍ ግማሹን እንኳ ለመመደብ አልታደለችም። እናም ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ በቀጣይ ይደረጋል የሚለው ከሆነ ጥሩ ነው። በመልካም ጎኑ እናየዋለን። 
ግን በጀት መመደቡ በጤና ባለሙያው የሚያመጣው ኢምፓክት ነው መታየት ያለበት።
ጤና ተቋማትን ለማስገንባት፣ ማሽነሪዎችን ለማስገባት የተደረጉ ነገሮች አሉ እናደንቃለን። ግን የጤና ባለሙያውን እርካታ ሊጨምር የሚችለውን ኢምፓክት አልተነሳም፤ መነሳት ነበረበት።
በቃለ ምልልሱ ሪፎርሙን ሳይሆን ባለሙያው አንገብጋቢ 12 ጥያቄዎች አሉት ሊመሱለት የሚገባ፤ እነዛን ነበር አድሬስ ማድረግ የነበረባቸው። ስለዚህ ገለጻው ለጥያቄያችን ምላሽ ነው ብለን ለመውሰድ ያስቸግረናል ” ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
All Articles