June 17, 2026

በምርጫው ድሬዳዋ ውስጥ የግል ተወዳዳሪ ሆነው ቀርበው የነበሩት ዶክተር ሀብታሙ ዓለሙ በዛሬው ዕለት መታሰራቸው ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- በድሬዳዋ-1 የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግል እጩነት ቀርበው የነበሩትና በወቅቱ በነበረው የምርጫ ሂደት ላይ እምነት ማጣታቸውን ገልፀው ራሳቸውን ማግለላቸው አስታውቀው የነበሩት ዶክተር ሀብታሙ ዓለሙ ሸዋ ዛሬ ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ሥራ ቦታቸው በመጓዝ ላይ እያሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።

ዶክተር ሀብታሙ ከመታሰራቸው ከማለዳው እለት ጀምሮ በቤተሰባቸው ላይ ያነጣጠረ እስርና እንግልት እየተፈጸመ መሆኑን በመቃወም ለብዙኃን መገናኛዎች ድምፃቸውን ሲያሰሙ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ግን እሳቸው ራሳቸው በቤተሰባቸው መኖሪያ ቤት ፊት ለፊት በጸጥታ ኃይሎች ተከበው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የመረጃ ምንጮች ለሚድያችን ጠቁመዋል።

የጸጥታ አካላት ዶክተር ሀብታሙን ከያዙ በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ፍተሻ ያካሄዱ ሲሆን ለምርመራ ያግዛሉ የተባሉ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን እና ሌሎች የግል የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎቻቸውን በሙሉ አብረው መውሰዳቸውን የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

ዶክተር ሀብታሙ ዓለሙ ሸዋ ከመታሰራቸው ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ ለሚዲያዎች በላኩት እና አሁን ላይ ይፋ በሆነው አስቸኳይ መልዕክት ታላቅ ወንድማቸውና የሁለት ልጆች አባት የሆነው አቶ አሰግድ ዓለሙ ትላንት ሰኞ ጠዋት ከሥራ ቦታው በስልክ ተጠርቶ በቁጥጥር ስር መዋሉን በዝርዝር አስረድተው ነበር።

እንደ ዶክተር ሀብታሙ ገለጻ ወንድማቸው ምንም ዓይነት ሕገ-ወጥ ድርጊት ሳይፈጽም በድሬዳዋ ፖሊስ የታሰረ ሲሆን መኖሪያ ቤቱም ያለ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ እንደ አሸባሪ መበርበሩን ገልጸዋል።

ፖሊስ አቶ አሰግድን በቁጥጥር ስር አውሎ እየጠየቀ ያለው "መንግስትን የሚቃወም ፖለቲከኛ ወንድም አለህ ወይ" በሚል መነሻ እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር ሀብታሙ ይህ እርምጃ በእሳቸው የፖለቲካ አቋም እና ቀደም ሲል በነበራቸው የምርጫ ተሳትፎ ምክንያት ቤተሰባቸውን ለቂም በቀል፣ ፍርሃት ለመንዛት እና ኃይልን ለማሳየት የታለመ ነው ሲሉ በጽኑ አውግዘዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዶክተር ሀብታሙ ዓለሙ መታሰር ቀደም ሲል በድሬዳዋ ከተማ ከነበረው ውጥረት የነገሠበት የፖለቲካ ምሕዳር ጋር የተያያዘ መሆኑን የቅርብ ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ዶክተር ሀብታሙ በወቅቱ በግል እጩነት በነበሩበት ወቅት የድሬዳዋ የጸጥታና ፍትህ አካላት የሕግ ጥሰት እየፈጸሙ ነው በሚል እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአቤቱታቸው ተገቢውን ምላሽ አልሰጠም በማለት ከምርጫው ራሳቸውን በይፋ ማግለላቸው ይታወሳል።

በወቅቱ በሰጡት መግለጫ ደጋፊዎቻቸው እና ጓደኞቻቸው ሆን ተብሎ እንዲታሰሩ መደረጉን፣ ዋስትና መከልከላቸውን እና ሕዝቡ እሳቸውን እንዳይደግፍ የማስፈራራት ሥራ መሠራቱን አጋልጠው የነበረ ሲሆን አሁን የተፈጸመው እስርም የዚሁ ቀጣይነት ያለው የፖለቲካ ጫና አካል ሳይሆን እንዳልቀረ በሰፊው እየተነገረ ይገኛል።

| መሠረት ሚድያ | https://www.meseretmedia.org/p/026

All Articles