ይህ ትግል የግለሰቦች የግል ጉዳይ አይደለም። እኔ በበኩሌ ዶ/ር ደረጄ በጣም ጥሩ ሰው እንደሆነ አውቃለሁ፣ በማእረግ የተመረቀ ጎበዝ ሀኪምም እንደሆነ አውቃለሁ። በጣም የምወደው ለቦታው የሚመጥን የበፊት አለቃዬም ነው።ዶ/ር ደረጄ ብቻውን ሊፈታው የሚችለው ነገር እንደሌለም እንረዳለን። እኛ ስንታገል ግን ግለሰቦችን ወይንም ደግሞ የሆነ የፖለቲካ ፖርቲን አይደለም የምንታገለው። የምንታገለው የጤና ባለሞያን፣ ሀኪምንና ህክምናን ያዋረደን የኢትዮጵያን የጤና ስርዓት እንዲሁም የበጀት ድልድልን ነው።
እዚህ ጥያቄ ውስጥ ተሸናፊና አሸናፊ የለም። ህክምና ሲቆም እንደሀገር ሁላችንም ተሸናፊዎች ነን። ደሀ ሲሰቃይ እና ሲታረዝ ሁላችንም ተሸናፊዎች ነን። ለዚህም ነው ባለሞያው አስቀድሞ ለሀይማኖት ተቋማት የንስሀ ደብዳቤ ያስገባው። ለባለሞያው የተሰጠው ብቸኛው አማራጭ ግን ሁሉንም ተሸናፊ የሚያደርግ ስራ ማቆምን እንዲመርጥ አድርጎታል። ባለሞያው የስራ ማቆምን ጉዳት ስለሚያውቅ ይህ እንዳይሆን ለአመታት እየሰራ ታግሏል። ጥያቄውን ግን የሚመለከተው ጠፋ።
ባለሞያው ሀላፊነት ተሰምቶት ስራውን እየሰራ በጠየቀ ጊዜ ማን መልስ ሰጠው? አሁንም ቢሆን ባለሞያው ስራ ማቆሙ እንዲቀጥል አይፈልግም። የሚፈልገው ሁላችንም ከምንሸነፍበት ወጥተን ሁላችንም ወደምናሸንፍበት መንገድ መውጣትን ነው። ለዚህ መፍትሄው ደግሞ ባለሞያውን እያሰሩና እያስፈራሩ ለበለጠ አመፅና ጥላቻ መጋበዝ ሳይሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደራድሮ ጥያቄውን መመለስ ነው።
እኔ ከበላሁ ሰርዶ አይብቀል የሚሉ፣ የግል ሁኔታቸው የተመቻቸላቸው ሲኒየር ሀኪሞች ለኛ ዘመን ጥያቄ አለመመለስ እና የጥያቄው መታፈን ምክንያት ነበሩ። መቼም ከግል ሁኔታ ወጥተው ለሞያ ክብርና ለቀጣይ የሀኪም ትውልድ አይጨነቁም፣ አብረው መታገል ሲገባቸው ሬዝደንትና ኢንተርንን በማስፈራራት ጥያቄውን ያሳፍናሉ። እኔ በበኩሌ የተመቻቸ ነገር ላይ ነው ያለሁት፤ ነገር ግን የልጅነት ልፋቴንና ሀገሬ ላይ ተስፋ እንድቆርጥ ያረገኝን ነገር አረሳውም። እነዚህን በአንድነት ቆሞ መታገል ያስፈልጋል። የሞያ ጓደኞቼ እና ታናናሾቼ በሞያቸው ኮርተውና ተከብረው ሀገራቸው እንዲኖሩ እመኛለሁ። ለዚያም አብሬ እቆማለሁ።
ህብረተሰቡም ሆነ መንግስት የሀኪምን ድካም፣ ጥረትና ዋጋ ሚተምነው ፈልጎ ያጣው ቀን ነው። በጅ ያለ ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል እንዲሉ ሞያህንና ልፋትህን በረከሰ ዋጋ እንዲበዘብዙ አትፍቀድላቸው።
ሰባት አመትና ከዛ በላይ ቀን ከሌት አጥንቶና ለፍቶ የከበረውን የህክምና ሞያ የያዘ ሰው ከባጃጅ ሹፌርና ከሊስትሮ በታች እንዲኖር የፈረደ መንግስትም ይሁን ህዝብ ለሚፈጠረው ችግር እራሱን ተጠያቂ ያድርግ። ዛሬ ሀኪሞች ሲታሰሩ እንደድራማ ፀጥ ብለህ ያየህ ህዝብ ነገ ሀኪም ሳታጣ ማንን ልትወቅስ ይሆን? ከዚህ በኋላ ባለሞያው በዓላማና በዓንድነት ከፀና፣ ቀጣይ ጥያቄውም፣ ሰላማዊ ሰልፉም የህዝቡ ነው።
ዝለዚህ ለውጥ ከፈለጋችሁ በዓላማ ፅኑ፣ ትግሉን ከግለሰብ ላይ አውርዳችሁ ስርዓቱ ላይ አድርጉ። እስቀመጨረሻው አንድ ከሆንን ምንም አማራጭ ስለሌላቸው ጥያቄችያንን ይመልሳሉ።
ለመንግስት ደግሞ፣ እንደህፃን እልህ ከመግባት ወጥታችሁ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን መንገድ አስቡ። crisis management ክህሎትን ተጠቀሙ እንጂ እንደወጠጤ ጎረምሳ ለችግር ሁሉ መፍትሄ ዱላና ጉልበትን አትጠቀሙ። ልክ ኮሮና ሲመጣ ለጤናው ሴክተር አስቸኳይ የበጀት ስብሰባ (budget re-allocation and emerged budget mobilization) እንደተደረገው ይህም የጤናው ዘርፍ እንደድንገተኛ አደጋና ወረርሽኝ መቆጠር ያለበት በመሆኑ፤ በጊዜ ካልተፈታ የጤና ስርአቱም ሆነ ህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚያደርስ ጉዳይ እንደሆነ ተገንዝባችሁ በዛው ልክ ወደስራ ግቡ። emergency preparedness and response resources activation (የአደጋ ጊዜ ዝግጁነትና ምላሽ ቡድንን እንዲሁም ግብዓትን) ተጠቅማችሁ ከባለሞያው ጋር ተደራደሩ። (You should always de-escalate as a government and never escalate as you are doing right now with imprisonment)የበለጠ አደጋና የህዝብ ቁጣ ሳይመጣ ችግሩን በመፍታት የመንግስትነት ወይም ደግሞ የፖለቲካውን የበላይነት መውሰድ ትችላላችሁ። ሁላችንንም ተሸናፊ ከመሆን የማትረፍ የምትችለዎ የቼዝ ጨዋታ የመንግስት እጅ ናት።
ዶ/ር አብርሃም ታሪኩ