(መሠረት ሚድያ)- የጤና ባለሙያዎች ተባብሶ ቀጥሏል ባሉት እስራት እና እንግልት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ስራ የማቆም እርምጃ ለመውሰድ ንግግር መጀመራቸው ታወቀ።
በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ሲጠይቁ የነበሩት እነዚህ የጤና ባለሞያዎች እስራትና እንግልት እየተካሄደባቸው መሆኑን በመግለፅ ይህን በማስመልከት ከታቀደለት ቀን በፊት ሙሉ በሙሉ ስራ ማቆም ለማወጅ ውይይት እንደጀመሩ መሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
ባለሙያዎቹ ትናንት የጀመሩት ሃገር አቀፉ የከፊል ስራ ማቆም አድማ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን መያዙን ተከትሎ የአንዳንድ የመንግስት ሆስፒታሎች አመራሮች ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን በዛሬው እለት ብቻ ወደ 10 የሚጠጉ የጤና ባለሞያዎችን ከቤታቸው እና ከስራ ገበታቸው አስነስተው ለእስር እንደዳረጉ ታውቋል።
ከታሰሩት ባለሞያዎች መሃል ጠቅላላ ሃኪሞች፣ ኢንተርን ሃኪሞች፣ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቶችና ሬዝደንቶች፣ ነርሶች እና የላቦራቶሪ ባለሞያዎች ይገኙበታል ተብሏል።
በተለያዩ ሆስፒታሎች የስራ ማቆሙን ባላማከለ መልኩ የሆስፒታሉ ሰራተኞች ወደ ስራ ካልተመለሱ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የሚዝት ማስታወቂያ ከአስተዳደር በየግቢው ተለጥፏል ብለው ለሚድያችን ቃላቸውን የሰጡ የእንቅስቃሴው አስተባባሪዎች የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አስተዳደር በተጠባባቂነት የተያዙ ሃኪሞችን ከነገ ጀምሮ የሰው ሃብት ቢሮ በመምጣት እንዲመዘገቡ ማስታወቂያ አውጥቷል ብለዋል።
"ጠዋት ላይ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አመራሮች ጋር ተገናኝተው መንግስት ጉዳዩን በተለያዩ መንገዶች እንደሚይዘው ጠቅሰዋል። በዋነኝነም ስራ እያቆሙ ያሉ ሰራተኞችን ስም ዝርዝር ተቀብሎ በማባረር በአስቸኳይ ቅጥር ማረግና ጥብቅ የሆነ አቴንዳንስ እንዲያዝ፣ ጥያቄዎቹን በተመለከተ በሂደት እንዲሚመለስ፣ ከዚህ ባለፈ ተቃውሞ እናረጋለን የሚሉትን የፖለቲካዊ ጥያቄ በማንሳት መጠቀሚያ ናቸው ብሏል" በማለት ምልከታቸውን አጋርተዋል።
"ጥያቄው የቅንጦት ወይም የስልጣን ወንበርን የመነቅነቅ ጉዳይ እንዳልሆነና ባለሞያው በቂ ከፍያ እየተከፈለው ስራ እንዲሰራና ህዝቡን እንዲያገለግል የመጠየቅ መሆኑን እየገለጸ፣ መብቱን የሚጠይቅ ባለሞያን ማሰርና ማንገላታት ህገመንግስታዊ አለመሆኑን እና ሰብአዊ መብጽ የሚጋፋ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ሰራ ማቆም ከታቀደለት ቀን በፊት ሊታወጅ እንደሚችል ይገልጻል" በማለት አቋማቸውን ለመሠረት ሚድያ አጋርተዋል።
ዛሬን ጨምሮ በስራ ማቆም ላይ ያሉ ሆስፒታሎች አለርት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ፔጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የካቲት 12 ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ፓውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ንግስት እሌኒ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ደብረ ብርሃን ሃኪም ግዛው ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ አሰላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጎቤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ሚዛን ቴፒ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ሚኒሊክ ሆስፒታል የአይን ክፍል፣ ቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ አዲስአለም ሆስፒታል፣ ፈለገ ህይወት ሆስፒታል፣ አክስታ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ አዲስዘመን ሆስፒታል፣ ዱርቤቴ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል፣ ጃልዱ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል፣ እንጅባራ፣ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ ደባርቅ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ ጃናሞራ ሆስፒታል፣ ዳባት ሆስፒታል፣ አዲርቃይ ሆስፒታል፣ ደሴ ሆስፒታል፣ መተማ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንዲሁም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መሆናቸው ታውቋል።
መረጃን ከመሠረት!