Healthcare workers preparing for second strike
Updates
00
D
:
00
H
:
00
M
:
00
S

"መሠረታዊ ፍላጎታችን ይሟላልን ብሎ በህጋዊና በጨዋነት መንገድ መጠየቅ ፖለቲካ ከሆነ የእውነትም ጥያቄያችን ፖለቲካዊ ነው።"

May 9, 2025
በህዝብ ዘንድ የሚነሱ የትኛውንም የመብት ጥያቄዎች የፖለቲካ ስም እየሰጡ ለማክሸፍ የሚኬድበት እርቀት በጣም የሚያስገርምና የሚያሳዝን፣እንደ ሀገርም የሚያሳፍር ነው።በእርግጥም ይህ የሚያሳየው ህቡዕ ምስጢር አለ።ይህም የመጀመሪያው የመብት ጥያቄ ያቀረቡ ሰዎችን በዚህ ስበብ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በአፍም፣በሰይፍም፣በሰደፍም አስፈራርቶ ለማሸማቀቅና ጥያቄያቸውን አድበስብሶ እና አዳፍኖ ለማስቀረት የሚሄዱበት መንገድ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በመሪነት ያሉት ባለሥልጣናት አቅመቢስና በራስ መተማመን የሌላቸው፣የበታችነት ስሜት የሚጠዘጥዛቸው እውቀትና አዋቂ ጠል መሆናቸውን የሚያመላክት ነው።ይህ ባይሆን ኖሮ እርቦናል የዳቦ መግዣ፣ታርዘናል የልብስ መግዣ፣በርንዳ ላይ ማደር ጀምረናል የቤት ክራይ የምንከፍለው(ቤት እንግዛ አላልንም) የደመወዝ ማሻሻያ ይደረግልን። ስንታመም የምንታከምበት የጤና መድኅን ዋስትና ይሰጠን፣ለአገልግሎት እንዲፋጠን የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጠን፣የህብረተሰቡ ጤና እንዲጠበቅ (እናት በወሊድ ምከንያት እንዳትሞት) የጤና ስርዓቱ ይስተካከል ብሎ መጠየቅ ምኑ ነው ፖለቲካ የሚሆነው።ለሀገር እድገትና ለህዝብ አገልግሎት የሚገደው ሀገረ መንግሥት ቢኖር ኖሮ እኛ በአደባባይ እርቦናል ብለን ከመውጣታችን በፊት ምን ጎደለ ብሎ ጠይቆ የእኛንም የህብረተሰቡንም ችግር ቀድሞ በቀረፈ ነበር።ይህስ ይቅር መቼም አልታደልንም። ቢያንስ እንዴት የአንዲት ሀገር ህዝቦች የጤና ዋስትና የሆነ የማህበረሰብ ክፍልና አንቱ የተባለ ምሁር ክብሩን ትቶ፣ኀፍረትንም ከህሊናው ገፍቶ ጥሎ በአደባባይ እርቦናል እርዱን ብሎ በጨዋነት የእሮሮ ድምጹን ሲያሰማ እንዴት ጆሮ ይነፈገዋል?እንዴት አልተራብክም ይባላል?ጭራሽ ፓለቲካ ነው ብሎ ለማሸማቀቅ መሞከርስ ምን አይነት ህሊና ቢስነት ነው።ለመሆኑ ፖለቲካ ምንድን ነው? ፖለቲካዊ አጀንዳስ?እርቦናል፣ታርዘናል፣መኖሪያ አጥተናል፣ታመን መታከሚያ የለንም ማለት ነውን የፖለቲካ አጀንዳ?መንግስት ሆይ መኖር አቅቶናል፣የምናገኘው ገቢና የኑሮ ውድነቱ አልመጣጠን ብሎ ለምንሰጠውም የህዝብ አገልግሎት እንቅፋት እየሆነብን ነው ስለዚህ "መሠረታዊ ፍላጎታችን ይሟላልን ብሎ በህጋዊና በጨዋነት መንገድ መጠየቅ ፖለቲካ ከሆነ የእውነትም ጥያቄያችን ፖለቲካዊ ነው።"
በመጨረሻም :-
✍️እናንተ የመንግስት ባለስልጣናት ሆይ ምንም እንኳን እናንተ ጉንፋን ሲያማችሁ እንኳን ውጭ እየሄዳችሁ የምትታከሙ (በሀገርና በህዝብ ንብረት መሆኑን ልብ ይሏል) ብትሆኑም ለዚህ ላበቃችሁ ህዝብ ስትሉ የጤና ባለሙያውን ጥያቄ በተገቢው ሁኔታ መልሱለት።ይህን አለማድረግ ህዝቡ በደዌ እንዲሞት በህግ አዋጅ እንደማጽደቅ ነው፣ወይም በአጭሩ የሞት ፍርድ እንደመፍረድ ነውና።
✍️እናንተ የፖለቲካ አክቲቪስቶች ሆይ እንጀራችሁን ለማብሰል ብላችሁ የጤና ባለሙያውን ጉሮሮ ከማነቅና ጥያቄውን ሌላ መልክ ከመስጠት ተቆጠቡ።
✍️እናንተ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎችና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሆይ ከዚህ በፊት በነበረው ቢሉ አሁንም ባለው አስከፊ ጦርነት ወቅት የጥይት ናዳ በላያቸው ላይ እየወረደ የእናንተን ሕይወት ለመታደግ ሕይወታቸውን አሳልፈው ለሰጧችሁና በፈጣሪ እረዳትነት ሕይዎታችሁን አትርፈው እዚህ ላደረሷችሁ፣ወደፊትም በሚታደጓችሁ የጤና ባለሙያዎች ላይ እጆቻችሁን በትር ለማንሳት፣ሰንሰለት ለማስገባት፣ቃታ ለመሳብ እንዳትሞክሩ። ይህ ቀን አልፎ እንተዛዘባለንና።
✍️እናንተ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሆይ ከፈጣሪ በታች እናንተን የሚፈውሱ እጆች ቸግሯቸው በአደባባይ ተዘርግተዋል። እነዚህ ፈዋሽ እጆች አመድ አፋሽ ሆነው በባዶ ከተመለሱ እናንተን ለማከምና ዳሶ ለመፈወስ ወደ ጤና ተቋማት አይመለሱምና ስለራሳችሁ ጤና እና ደህንነት ስትሉ ከጤና ባለሙያው ጎን እንድትቆሙ።
እመኑኝ ዛሬ እኛ እራበን ስንል አልተራባችሁም ለሚለን አካል ነገ ታሞ ቢመጣ አልታመምክም ብለን እንደምንመልስ ቃላችን ነው።
ህመሙን ህመማችን አድርገን የኖርንለት ሀገርና ህዝብ ህመማችን ህመሙ ካልሆን እኛስ ለማን ብለን የሰው ህመም እንሸከማለን?
" መሠረታዊ ፍላጎታችን ይሟላልን ብሎ በህጋዊና በጨዋነት መንገድ መጠየቅ ፖለቲካ ከሆነ የእውነትም ጥያቄያችን ፖለቲካዊ ነው።"
በአንድነት ወደፊት
4 Days Left